ናሬንድራ ሞዲ ለአርሶ አደሮች የ2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 6 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ ለአርሶ አደሮች የ2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አድርገዋል፡፡
ድጋፉ በሀገሪቱ 80 ሚሊየን የሚደርሱ አርሶ አደሮችን ለመርዳት የተዘጋጀው የበጎ አድራጎት መርሐ ግብር አካል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ይፋ የተደረገው ድጋፍ በዲጂታል ባንኪንግ አማካኝነት በቀጥታ ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደር ሒሳብ ገቢ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ድጋፉ ይፋ የተደረገበት ጊዜ በሀገሪቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ ነው የተገለጸው፡፡
ፓርቲዎቹ ድጋፉ በሀገሪቱ በ2024 ለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫው ወሳኝ የሚባሉ ግዛቶች ምርጫ ከማካሄዳቸው ሁለት ቀናት በፊት ይፋ መደረጉ ትክክል አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ድርጊቱ በምርጫ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩ ባለፈ የሀገሪቱን የምርጫ ሕግ እና ደንብ የጣሰ ነው ማለታቸውንም አር ቲ ዘግቧል፡፡
ድጋፍ ምርጫው መቃረቡን ተከትሎ ይፋ መደረጉም በምርጫው አትራፊ ለመሆን በገዢው ፓርቲ ሆን ተብሎ የተቀናበረ ድርጊት እንደሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላላ ምርጫው መቃረቡን ተከትሎ ናሬንድራ ሞዲ እስካሁን በጫካ ውስጥ የሚኖሩ የጎሳ አባላትን በ22 ሺህ መንደሮች ለማስፈር አስፈላጊው ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡