የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 164 ቢሊየን ዶላር ገደማ ደርሷል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ጫናዎች ውስጥም ሆነንም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ5 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በእጥፍ አድጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በምላሻቸውም÷ እንደሀገር ከተያዙት ሁነኛ ግቦች መካከል÷ የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ ኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢን ማዘመንና ማሻሻል፣ የዘርፎች ምርታማነትን ማሣደግ እንዲሁም የመንግሥትን ዐቅም ማሣደግ የሚሉት እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
ከ’ግሬይ ወደ ግሪን’ ኢኮኖሚ ማሣደግን ታሳቢ በማደርግ መንግሥት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለያዩ ጫናዎች ውስጥም ሆነንም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ5 ዓመታት ውስጥ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በእጥፍ አድጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ84 ቢሊየን ዶላር ወደ 164 ቢሊየን ዶላር ገደማ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ የተነገረ መረጃ ሳይሆን በዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የተረጋገጠ ስለመሆኑ በማብራሪያቸው አንስተዋል።
የነፍስወከፍ ገቢያችንም 882 ዶላር ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ አሁን 1 ሺህ 549 ደርሶ በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗንም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
በዮሐንስ ደርበው