የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን ካለፈው ዓመት ጀምሮ የ27 ቢሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉ ተሰማ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ካለፈው አመት ጀምሮ የ27 ቢሊየን ዩሮ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጉን የህብረቱ የውጭ ጉዳይና ፀጥታ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ገለጹ።
ቦሬል በቤልጂየም ብራሰልስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አባል ሀገራቱ ካለፈው አመት ጀምሮ ለኪየቭ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወታደራዊ ድጋፉን ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
በመግለጫቸው ምንም እንኳን በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ግጭት ቢቀሰቀስም ሀገራቱ ለኪየቭ የሚያደርጉትን ድጋፍ “አይረሱም” ብለዋል።
“ለዩክሬን የምናደርገው ድጋፍ እየጨመረ ነው” ያሉት ጆሴፍ ቦሬል “አሁን ላይም የተደረገው ወታደራዊ ድጋፍ 27 ቢሊየን ዩሮ” መድረሱን አስረድተዋል።
ይህ አሃዝ ከፍተኛው መሆኑን ያነሱት ቦሬል የዩክሬን ወታደሮችን ማሰልጠናቸውን እንዲሁም ከዩክሬን ጎን መቆማቸውን እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት።
በተያያዘም ህብረቱ ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት አግባብ ላይ ለመምከር ማቀዱን አር ቲ በዘገባው አስነብቧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንድ ሀገራት ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ እዚህ ላይ መቆም አለበት የሚል አቋም እያንጸባረቁ ነው ተብሏል።
ጀርመን፣ ስሎቫኪያ እና ፈረንሳይ ለዩክሬን ይደረግ እየተባለ ባለው ተጨማሪ ድጋፍ ተግባራዊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ፈረንሳይ በበኩሏ ለኪየቭ ተጨማሪ ድጋፍ ከማደርግ ይልቅ ‘በልዩ ፈንድ’ ወታደራዊ ቁሳቁስ ከግል ኩባንያዎች ብገዛ እመርጣለሁ ማለቷም ተሰምቷል።