Fana: At a Speed of Life!

በዚህ ዓመት ከ800 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው ዓመት ከ800 ሚሊየን በላይ ኩንታል ለማምረት በሥፋት እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ÷ በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ያለፈው ዓመት የግብርና ዘርፍ ዕድገት 6 ነጥብ 3 በመቶ መሆኑን አስታውሰው÷ በተለይ የሰብል ምርት 7 ነጥብ 1 ገደማ ማደጉን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከ20 ሚሊየን ሔክታር በላይ በማረስ ከ600 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም ነው ያስታወሱት፡፡

በዚህ ዓመትም ከ22 ሚሊየን ሔክታር በላይ በማረስ ከ800 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በስፋት እና በትጋት እየተሠራ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችም የያዝነውን ዕቅድ እንደምናሳካ ያመላክታሉ ብለዋል፡፡

በበጋ ወቅትም 3 ሚሊየን ሔክታር በመስኖ ልማት በስንዴ ለመሸፈን መታቀዱን ነው የጠቆሙት፡፡

ለተያዘው ዕቅድ መሣካት አርሶ አደሩ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ርብርብ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

በዮሐንሰ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.