የሰሞኑ ጉንፋን መሰል ህመምና ጥንቃቄዎቹ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ጉንፋን መሰል ህመም በስፋት እየተዛመተ ይገኛል፡፡
በቅርቡ የተከሰተውን ጉንፋን መሰል ህመምና ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች አስመልክቶ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ አስተባባሪ ዶ/ር ግዛው ተካ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
እንደ ዶ/ር ግዛው÷ የክረምት ወራት ወይም የዝናብ ወቅት ማብቃቱን ተከትሎ በጥቅምትና ህዳር ወራት እንደዚህ አይነት ጉንፋን መሰል ህመም የሚጠበቅ ነው፡፡
ህመሙ ጉንፋን መሰል ቢሆንም ለየት የሚያደርገው ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ሊቆይ እንደሚችልና ከ39 እስከ 39 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴሊሸየስ የሚደርስ የሙቀት መጠን በተለይ በልጆች ላይ እንደሚያሳይ ነው ያመላከቱት፡፡
ምልክቶቹም እንደ የአፍንጫ ፈሳሽ መብዘት፣ ሳል፣ ራስ ምታትና ጉሮሮን ማቃጠል ከፍ ሲልም ድካምና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መሰል ህመም ተሰምቷቸው ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት ናሙና ከሰጡት ውስጥ የኢንፍሉዌንዛና ጉንፋን ተጠቂዎች ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በዚሁ ወቅት የተከሰተው ጉንፋን መሰል ህመም በተለይ በህጻናት ላይ በብዛት የተከሰተ ሲሆን ወቅቱ ትምህርት ቤት የተከፈተበት በመሆኑ ከፍተኛ መስፋፋት ታይቶበታል ብለዋል፡፡
አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ ህመሙ የመዛመት እድሉ ከፍ ሊል እንደሚችል ያሳሰቡት ዶ/ር ግዛው፤ በተለይ ቀዳሚ ተጎጅ ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ህጻናትና አረጋዊያን ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸውን ሰዎች ጥንቃቄ ልናደርግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ይህንን ጉንፋን መሰል ህመም ከምንከላከልበት መንገድ መካከልም የእጅ ንጽህናን በመጠበቅ፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ የአፍና አፍንጫ ጭምብል በማድረግና ምልክቱ ከታየም በቂ እረፍት ማድረግን ጨምሮ ፈሳሽ መውሰድ እንደሆኑ አመልክተዋል።
በተጨማሪም÷ ህመሙ በቤት ውስጥ በምናደርጋቸው ክትትሎች ለውጥ ካላሳየና ከፍተኛ ህመም ካስከተለ ወደ ጤና ተቋም ማምራት እንደሚገባም ዶ/ር ግዛው ይመክራሉ፡፡
በወንድሙ አዱኛ