ስዊዘርላንድ የኒውክሌር ኃይል የመጠቀም እቅዷን እንደምታራዝም ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አውሮፓዊቷ ሀገር ስዊዘርላንድ በኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ያሉ ሁሉም መሣሪያዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ እስከሆነ ድረስ ሥራቸውን ይቀጥላሉ ስትል ገልፃለች፡፡
ስዊዘርላንድ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ስጋት እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የኒውክሌር ኃይል አጠቃቀምን የማራዘም አዝማሚያ እየተስተዋለ መሆኑን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ እስከ 40 በመቶ የሚደርሰውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ አራት የኒውክሌር ኃይል ማብላያዎች እንዳሏት የዓለም ኒውክሌር ማህበር አስታውቋል።
ስዊዘርላንድ በፈረንጆቹ 2017 የኒውክሌር ኃይልን ለማስወገድ ወስና የነበረ ቢሆንም ጣቢያውን ለመዝጋት ግን ቀነ-ገደብ አለማስቀመጧን አር ቲ አስነብቧል።
ይሁን እንጅ ማመንጫ ጣቢያዎቹ ደህንነታቸው የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ በስራ ላይ እንዲቆዩ ወስናለች ነው የተባለው።
የኃይል አቅርቦት ቀውስ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ስጋት የስዊስ ኩባንያዎች የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን አገልግሎት ዕድሜ እንዲያራዝሙ እንዳነሳሳቸውም ነው የተመላከተው፡፡
የሃገሪቱ ግዙፍ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የሆኑት አክስፖ እና አልፒክ የተሰኙት ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም የኒውክሌር ኃልን ለ50 ዓመት ለመጠቀም የወጠኑትን ዕቅድ 10 ዓመት በመጨመር ለ60 አመታት እንዲሆን መወሰናቸውንም ነው ዘገባው ያመላከተው።
ይህን ተከትሎም ኃይል ማመንጫዎቹ እስከ ፈረንጆቹ 2040 ድረስ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል።
አሁን ላይ በአውሮፓ ያለው የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እና ፊንላንድ የኒውክሌር ኃይል መጠቀምን ለተጨማሪ አመታት የማራዘም ዕቅድ እንዳላቸው እየገለጹ ነው።