Fana: At a Speed of Life!

የምዕራባውያን ማዕቀብ ሩሲያ የራሷን አቅም እንድታሳድግ ዕድል ፈጥሯል – ዲሜትሪ ፔስኮቭ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ሞስኮ የራሷን አቅም በሚገባ እንድትጠቀም አስችሏታል ሲሉ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ገለጹ፡፡

ቃል አቀባዩ የምዕራባውያን ሀገራት ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ በሞስኮ ላይ የጣሉት ዘርፈብዙ ማዕቀብ መልካም እድሎችን ይዞ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

ማዕቀቡ ሞስኮ ሀገር በቀል እውቀቶችን በትኩረት በመጠቀም ከውጪ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በራሷ አቅም እንድትተካ አስችሏል ነው ያሉት፡፡

ሩሲያ የተጣለባትን ዘርፈ ብዙ ማዕቀብ መቋቋም መቻሏም ምዕራባውያንን ክፉኛ ማስደንገጡን አንስተዋል፡፡

በአንጻሩ ማዕቀቡ በምዕራባውያን ሀገራት ኩባንያዎች ላይ 250 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ማድረሱን ነው ያስረዱት፡፡

ከዚህ ባለፈም የአውሮፓ ሀገራት ከሩሲያ ጋር የነበራቸው የነዳጅ ንግድ ግንኙነት መቋረጥ ሀገራቱ ለአሜሪካ ውድ የሃይል አቅርቦት ጥገኛ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል ብለዋል፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው÷የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ ሞስኮ ከምዕራባውያን ጫና ነጻ የሆነ የንግድ ሥርዓት እንደምትገነባ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም አዳዲስ የንግድ ኮሪደሮችና የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ለማቋቋም እንደወሰነች መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.