ኦክሽን ኢትዮጵያ የተሰኘ የዲጂታል ጨረታ ሽያጭ መተግበሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ኦክሽን ኢትዮጵያ” የተሰኘ የዲጂታል ጨረታ ሽያጭ መተግበሪያ ዛሬ በይፋ ወደ ሥራ ገባ።
መተግበሪያው የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች በጨረታ መሸጥ የፈለጉትን ንብረት በዲጂታል መንገድ እንዲከውኑ የሚያስችል ምኅዳር መሆኑን የኦክሽን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዮሴፍ አንኩ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አሥፈጻሚው÷ በተመቻቸው ዲጂታል ምኅዳር ተጠቃሚዎች የትም መሄድ ሳይጠበቅባቸው በእጅ ሥልካቸው ወይም በኮምፒውተር ተጠቅመው ጨረታ መጫረት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ዘመኑ የዲጂታል እንደ መሆኑ መጠን የኋላ ቀር አሠራር ጊዜ እንዳለፈበት ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የንግድ ሂደቱ ተቀይሮ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሐብት ዕድገትና ከዓለም አቀፉ ሁኔታ ጋር ገደብ የለሽ ትሥሥር እና ዕድሎችን መፍጠሩን ገልጸዋል።
የ”ኦክሽን ኢትዮጵያ” የዲጂታል መተግበሪያም ይህን ዕድል የፈጠረ እና ምጣኔ ሐብቱ ላይ የበኩሉን ማበርከት የቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስትም መተግበሪያው በገበያ ውስጥ ገብቶ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያመጣ ድጋፍ እንደሚደርግ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶችም እንደ ሀገር የተያዘውን “ዲጂታል ኢትዮጵያ”ን የመፍጠር ጉዞ እንደሚያፋጥኑ ገልጸዋል።
ከሦስት ዓመታት በላይ በተደረገ ጥናትና ምርምር የበለጸገው መተግበሪያው፤ ዋና ትኩረቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ንብረቶችን በመግዛትና መሸጥ ሂደት ያለውን ችግር በመፍታት ፍትኀዊና ተደራሽ የሆነ የጨረታ ሥርዓትን መዘርጋት ነው ተብሏል።
በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ሰው “ኦክሽን ኢትዮጵያ”ን ተጠቅሞ የትኛውንም ጨረታ መሳተፍ እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡
በበረከት ተካልኝ