በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ በትግራይ ክልል የጤና ተቋማትን አገልግሎት የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት በኋላ በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማትን አገልግሎት የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊ አማኑዔል ኃይለ÷ በክልሉ በርካታ የጤና ተቋማት በጦርነቱ ሳቢያ አገልግሎት አቁመው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ በተለይም እናቶች እና ሕጻናት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የጤና ተቋማቱ በጦርነቱ ሳቢያ መደበኛ አገልግሎት አቋርጠው እንደቆዩና ከፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት በኋላ ግን በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ጥረት ዳግም ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይትም የጤና አገልግሎቶችን በተሻለ ደረጃ ለመሥጠት መቻሉን ገልጸው፤ በመንግስት በኩል የሚደረጉ ድጋፎች ለውጥ አምጥተዋል ነው ያሉት ኃላፊው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በክልሉ 79 ተጨማሪ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመልሶ ግንባታ ሥራው ከመንግስት ባለፈ የአጋር አካላት ተሳትፎ መኖሩን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፤ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡