Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ታላቁን የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በጉባ የሚገኘውን ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም ስለ ፕሮጀክቱ ከታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ከመከላከያ ሠራዊት ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ውሃው ተርባይኑን መትቶ ወደ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ እንደሚመለስና በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት የሚያመጣው ምንም ችግር እንደሌለ መመልከታቸውን ወታደራዊ አታሼዎቹ ገልጸዋል።

ከ97 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ በከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጦት የምትታወቀውን የአፍሪካ ልማት እንደሚያፋጥን ብሎም ለቀጠናዊ እና አኅጉራዊ የምጣኔ ሐብት ትሥሥር የራሱን በጎ ሚና እንደሚጫወት በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ ገና በጥቅም ላይ ያልዋሉ ዕምቅ የተፈጥሮ ሐብት እንዳላት የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና ግዙፉን የኅዳሴ ግድብ እውን ማድረግ መቻሏ በራሱ ሙሉ ለሙሉ የተሟላ ሰላም ካሰፈነች በፍጥነት ማደግ የምትችል ሀገር ስለመሆኗ ማሳያ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ጉብኝቱን ያመቻቸው የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ሲሆን ወደ 60 የሚጠጉ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በመርሐ-ግብሩ ተሳትፈዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.