ጀርመን እና ኢትዮጵያ የልማት ትብብር ድርድር ሊያደርጉ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ለሚያካሂዱት የልማት ትብብር ድርድር የቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ሥብሰባ ተካሄደ፡፡
በኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር የተካሄደው ሥብሰባ ዓላማ በፈረንጆቹ ኅዳር 27 እና 28 ለሚካሄደው ድርድር በጥልቀት ተወያይቶ ግልጽነትን በመፍጠር የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሥብሰባውን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮ-ጀርመን በኩል የልማት ትብብር ኃላፊ የሆኑት ቤንጃሚን ተድላ ሄከር መርተውታል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ በኩል የግብርና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር እንዲሁም የፍትኅ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጀርመን ደግሞ በኤምባሲዋ ፣ ኬ.ኤፍ ደብል ዩ በተሠኘው አበዳሪ ባንክ እንዲሁም የጀርመን ተራድዖ ድርጅት ተወክሏል፡፡
ጀርመን በሦስት ዘርፎች ማለትም በሠላም እና ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ የግብርና እና የምግብ ሥርዓት ለውጥ ፣ በዘላቂ የምጣኔ ሐብት ልማት እንዲሁም በሥልጠና እና የሥራ ፈጠራ ዘርፎች ላይ በትብብር መሥራት እንደምትፈልግ ረቂቋን አቅርባለች፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት ከየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ የወከሉት የሥራ ኃላፊዎችም የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።