Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያዩ።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተካሄደው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጨምሮ የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ልኡካን ተሳትፈዋል።

ውይይቱም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያልተቋጩ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ እና የተዛባ ግንዛቤ የነበረባቸውን ጉዳዮች ለማጥራት የታለመ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

በውይይቱም የአካባቢ ጥበቃ፣ የግድቡ የደኅንነት ሁኔታ እና የመረጃ ልውውጥን ስለ ማመቻቸት፣ በሱዳን በኩል ለተነሡት ጉዳዮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በውይይቱ ላይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ የሥራ ክንውኑ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል።

አክለውም፣ የሕዳሴው ግድብ ለሦስቱ የተፋሰሱ ሀገራት ኢኮኖሚ መጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የቴክኒክ ውይይቱን በሁለቱ ሀገራት የውኃ ሚኒስትሮች አማካኝነት ለመቀጠል ስምምነት ላይ መረደሱንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ውይይቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃም፥ “ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ለሁሉም አካላት በሚስማማ መፍትሔ ላይ መክረናል” ብለዋል።

የተሳሳተ ግንዛቤ የነበረባቸውን ጉዳዮች አጥርተን ተነጋግረናል፤ በውኃ ሚኒስትሮቻችን አማካኝነት የቴክኒክ ውይይቶችን ለመቀጠል እና ያልተቋጩ ጉዳዮችን አጠናቅቀን ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለመቀየስ ተስማምተናል” ሲሉም አስታውቀዋል።

“የሕዳሴው ግድብ ለሁሉም ሀገራት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለው እና በመተባበር ዕድሉን ልንጠቀምበት እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት አስረድቻለሁ” ሲሉም ገልፀዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.