Fana: At a Speed of Life!

በሰባቱ አመቱ ጦርነት የተጻፉ ደብዳቤዎች ከ265 ዓመታት በኋላ ተነበቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ አሁኑ ማሕበራዊ ሚዲያ ተደራሽ ባልሆበነበት ዘመን ሰዎች ሰላምታቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ ናፍቆታቸውንና ፍላጎታቸውን በወረቀት አስፍረው ለልባቸው ሰው እንዲደርስ በመልክተኛ ይልካሉ፡፡

መልዕክተኛው በቶሎ ካደረሰው እሰየው ብለው ምላሽን ይጠባበቃሉ ፤ ካላደረሰው ደግሞ የዚያኑ ያህል እረፍት ይነሳል፡፡

መልዕክታቸው የደረሰ እንደሆነም ምላሽ መጠበቁ በራሱ የዘላለም እድሜን ያክልባቸዋል ፤ ከወደዱት ሰው መራቅ ፣ የወደዱትን እንደልብ አለማግኘት፣ የተሰማን የፍቅርና የናፍቆትን ስሜት በአንድ ደብዳቤ አጭቆ መጻፍን ይፈትናል፡፡

በዚህ መልኩ ተጽፈው በጊዜው ለተላከላቸው ፈረንሳውያን ወታደሮች ሳይደርሱ የቀሩ 104 ደብዳቤዎች ከሰሞኑ ከ265 አመታት በኋላ ተከፍተው ተነበዋል።

ደብዳቤዎቹ በአብዛኛው ለታሰሩ የፈረንሳይ መርከበኞች የተላኩ እንደነበሩ ቢዝነስ ኢንሳይደር እና ቢቢሲ አስነብብዋል።

እነዚህ ደብዳቤዎች በወቅቱ በብሪታንያ እና በፈረንሳይ መካከል በተደረገው የሰባት አመታቱ ጦርነት በፈረንጆቹ 1757/58 ለፈረንሳውያን መርከበኞችና ወታደሮች የተጻፉ እንደነበሩ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሬናድ ሞሪዩ ይገልጻሉ።

ደብዳቤዎቹ በብሪታንያ ኬው ለንደን በሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ውስጥ ለታሰበው ሰው ሳይደርሱና ሳይነበቡ የቆዩ ሲሆን በመጨረሻም በታሪክ ተመራማሪው ተከፍተው ተነበዋል።

በወቅቱ ወታደራዊ ይዘት ሊኖራቸው ይችላል በሚል በእንግሊዝ ወታደሮች ተይዘው ቢቀመጡም ናፍቆትን ያዘሉ በርካታ ደብዳቤዎች እንደነበሩ ተማራመሪው ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ አን ለ ሰርፍ የተባለችው እመቤት ለባለቤቷ የጻፈችው የናፍቆት ደብዳቤ ይገኝበታል።

ደብዳቤው ‘’በልቤ ውስጥ ላለኸው ግን ላገኝህ ያልቻልኩት ውዱ ባለቤቴ በሚል ይዘት የተጻፈና የቆየ ናፍቆትና ፍቅሯን የገለጸችበት ነው።

“ውዱ ባለቤቴ ላንተ እየጻፍኩ ሌሊቱን ላነጋው እችላለሁ …እኔ ታማኟ ሚስትህ ማሪ ዱቦስክ ነኝ…’’ በሚል የተጻፈውና ለመጀመሪያዋ የፈረንሳይ የጦር መርከብ አዛዥ ያልደረሰው ደብዳቤም ከ265 አመታት በኋላ በታሪክ ተመራማሪው የተከፈተ ደብዳቤ ነው።

ይህ ደብዳቤ የተጻፈለት የጦር መርከብ አዛዥ ደብዳቤውም ሳይደርሰውና ከባለቤቱ ጋር ዳግም ሳይገናኝ ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ በሰሜናዊ ፈረንሳይ በጦርነቱ ህይወቱ አልፏል ነው የተባለው።

‘’ከአጠገቤ አለመኖርህን ልቋቋመው አልቻልኩም ፤ ቀናት ወራትን ወራት ደግሞ ዓመታትን እየወለዱ … ‘’ እና መሰል ይዘት ያላቸው ደብዳቤዎች ለተላኩለት ሰው ሳይደርሱ ከ265 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡

እነዚህ ደብዳቤዎች ለፈረንሳይ እስረኞች የተላኩ የፍቅርና የናፍቆት ደብዳቤዎች ናቸው፤ ሆኖም ደብዳቤዎቹ የያዙትና ሚስት ለባለቤቷ ቤተሰብ ለልጆቹ የላኳቸው ፍቅርና ናፍቆት ሳይነበቡና ምላሽ ሳያገኙ እስከወዲያኛው አልፈዋል፡፡

ከፈረንጆቹ 1756 እስከ 1763 በፈረንሣይ እና በብሪታኒያ መካከል የተደረገው ጦርነት በአሜሪካ መሬት ይገባኛል ምክንያት የተካሄደ ነበር።

በዚህ ጦርነት ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ፈረንሳውያን መርከበኞች በብሪታንያ ጦር ተይዘው የነበረ ሲሆን፥ ለእነዚህ እስረኞች ከፍቅር አጋሮቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የተላኩ ደብዳቤዎች ሳይደርሳቸው ወደእንግሊዝ ተመልሰው እንደተላኩም ነው የተነገረው፡፡

በወቅቱ ሁለት ደብዳቤዎችን ከፍተው ያዩት በጊዜው የነበሩት የእንግሊዝ ባለስልጣናት ደብዳቤዎቹ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው ከተገነዘቡ በኋላ እንኳን ለተላኩላቸው ሰዎች መስጠትን አልፈለጉም ነበር፡፡

ደብዳቤዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተው ያነበቧቸው ፕሮፌሰር ሬናድ፥ “የተጻፉላቸው ሰዎች ይህን እድል አላገኙም፤ ይሄ እጅግ ስሜታዊ ያደርጋል” በማለት የተሰማቸውን ገልጸዋል።

“እንደ ወረርሽኝ ወይም ጦርነት ከአቅማችን በላይ በሆኑ ክስተቶች ከምንወዳቸው ሰዎች በምንለይበት ጊዜ እንዴት መገናኘት እንዳለብን፣ እንዴት ማረጋጋት እንደምንችል፣ ሰዎችን እንዴት እንደምንከባከብ ማወቅና ስሜቱን መጠበቅ ይገባልም” ነው ያሉት።

#France #British #Letters

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.