በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን የሊቢያ አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንስ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊቢያ በደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንስ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ትናንት ተጀምሮ ዛሬም የቀጠለው ኮንፈረንስ የሚካሄደው በፈረንጆቹ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ የሊቢያን ከተሞች ያጥለቀለቀው ጎርፍ ካደረሰባቸው ጉዳት ያገግሙ ዘንድ መልሶ-መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር መሆኑን ዘ አረብ ዊክሊ ዘግቧል፡፡
ለሁለት ቀናት ሊካሄድ ቀን የተቆረጠለት ኮንፈረንስ በትናንትናው ዕለት በደርና የተጀመረ ሲሆን ዛሬም በቤንጋዚ ቀጥሎ መዋሉ ነው የተሰማው፡፡
በሁለቱ ቀናት ኮንፈረንስ ላይ በድምሩ 400 የሚደርሱ ተሳታፊዎች መገኘታቸውም ነው የተመለከተው፡፡
የኮንፈረንሱ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች በመሠረተ-ልማት ዝርጋታ እና በቤቶች ልማት ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተወካዮች እና ኩባንያዎች መሆናቸውን የሊቢያ መንግስት መግለጫ ያመላክታል።
የጎርፍ አደጋው በተከሰተበት ወቅት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።