Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሦስት ወራት ዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት መላኩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት ዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ይህን የገለፀው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዕቅድ አፈፃፀሙን ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው ።

ባሳለፍነው ሐምሌና ነሐሴ ወራት ከ500 በላይ የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንቶችን በመክፈት ከ699 ሺህ ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውንም ገልጿል።

በሩብ ዓመቱ ከዳያስፖራ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ በተደረገው ድጋፍና ክትትል ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ መላኩን አስታውቋል።

የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግም 250 የዳያስፖራ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ክትትል፣ ድጋፍና የማማከር ስራ ተሰርቷል ብሏል።

ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘም ከ 89 ሺህ በላይ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትን ያሳተፉና ወቅታዊና ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች የተዳሰሱባቸው የበይነ መረብ መድረኮችን እንደተካሄደ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህም ነባር የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩና አዳዲሶችም እንዲቋቋሙ ድጋፍ መደረጉንና የወጣት ዳያስፖራ አባላትን ሀገራዊ ግንዛቤና ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተግባራትም መከናወናቸውን አስታውቋል።

የዳያስፖራ አባላትንና አደረጃጀቶችን በማስተባበርም በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በደህንነትና ጥበቃ፣ በፋርማሲና ማኑፋክቸሪንግ፣ ዘርፎች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር መካሄዱም ተነስቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.