ዶላር አባዛለሁ በሚል ከአንዲት ግለሰብ 175 ሺህ ዶላር የወሰደው ተከሳሽ በ11 ዓመት እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዶላር አባዛልሻለሁ በሚል አንዲት ግለሰብን በማታለል 175 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የወሰደው ግለሰብ በ11 ዓመት እስራት ተቀጣ፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው ከሕዳር እስከ የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተለያዩ ቀናት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የካ አባዶ ጂ ሰቨን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
ልባዊ ገሰሰ የተባለው ተከሳሽ እና የግል ተበዳይ በአጋጣሚ ከተዋወቁ በኋላ የሚሸጥ መሬት ነበረኝ ገዢ አጣሁ ብላ ስትነግረው ይሸጣል እኔ እፀልይልሻለሁ ብሎ ይነግራትና ሚስጢሩ ግን ከእሷ ውጪ ማንም ጆሮ እንዳይደርስ ያስጠነቅቃታል፡፡
በሌላ ቀን ደውሎ መሬቱን በሁለት ሚሊየን ብር ለምን አትሸጪውም ብሎ ሲጠይቃት በሶስት ሚሊየን ብር ገዝቼ በኪሳራ ለምን እሸጣለሁ የሚል ምላሽ ትሰጠዋለች፡፡
በድጋሚ ጥር 14 ቀን 2014 ዓ.ም ደውሎ 5 ኪሎ አካባቢ ከቀጠራት እና ከተገናኙ በኋላ በባንክ ውስጥ ስንት ብር እንዳላት ይጠይቃታል፡፡
750 ሺህ ብር እንዳላት ስትነግረው ከባንክ አውጪው፣ ቤትሽንም ሽጪው፣ ገንዘብ የሚያበድርሽ ሰው ካገኘሽም ተበደሪ፣ ከዚያ ሁሉንም ብር ወደ ዶላር ቀይረሽ አስቀምጪው፣ ትክክለኛ ዶላር መሆኑን እኔ አረጋግጬ በረከት አወርድበታለሁ ብሎ ያግባባታል፡፡
የግል ተበዳይም ሃሳቡን ተቀብላ፣ የተባለችውን አምና ከጥቁር ገበያ እየገዛች 175 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ስታጠራቅም ቆይታ፤ይህንኑ ለተከሳሹ ትነግረዋለች፡፡
በመቀጠልም ተከሳሽ 321 ሚሊየን ዶላር ሆኖ እንደሚበዛላት እና ዶላሩን ማስቀመጫ የሚሆን ቁልፍ ያለው በርሜል እንድትገዛ እንደነገራት የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተከሳሽ ልባዊ ገሰሰ የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም የግል ተበዳይን ለማግኘት ወደ ቤቷ ይሄዳል፤ቤቷ ከደረሰ በኋላም ፀሎት ስናደርግ መተያየት የለብንም የሚል ምክንያት በማቅረብ አይኗን እና ፊቷን በጨርቅ እንድትሸፍን ያደርጋል፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር ለመፈፀም ያሰበውን ወንጀል ማሳካት የቻለው፡፡
የግል ተበዳይ በጥቁር ገበያ እየገዛች ያጠራቀመችውን 175 ሺህ ዶላር በወረቀት እየጠቀለለ ዶላሩ እንዲቀመጥበት ተብሎ የተገዛው ባለቁልፉ በርሜል ውስጥ የከተተ በማስመሰል ይዞ በመጣው ቦርሳ ውስጥ በመክተት እና በርሜሉን ቆልፎ ቁምሳጥን ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ቁልፉን ራሱ ጋር እንዲቀመጥ በማድረግ እና ከአንድ ወር ከ5 ቀን በኋላ ፀሎት አድርጎ ራሱ ብቻ እንደሚከፍተው ማሳሰቢያ በመስጠት ዶላሩን ይዞ ሊሰወር ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የግል ተበዳይን አቤቱታ ተቀብሎ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ልባዊ ገሰሰን በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ አቃቤ ሕግ በከባድ ማታለል ወንጀል ክስ መስርቶበታል፡፡
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ሰሞኑን በዋለው ችሎት ተከሳሹ በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
ተከሳሹ በማታለል ወንጀል ባገኘው ገንዘብ ባለ አንድ እና ባለ ሁለት መኝታ ቤት እንዲሁም ስቱዲዮ በአጠቃላይ ሶስት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የገዛ መሆኑ ተረጋግጦ ቤቶቹ ታግደው የፍታብሔር ክሱ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል ተብሏል፡፡