Fana: At a Speed of Life!

ኢራን ቀጠናዊ የጋዝ ማዕከል መገንባት እንደምትፈልግ አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን ቀጠናዊ የጋዝ ማዕከል መገንባት እንደምትፈልግ አስታወቀች።

የሃገሪቱን ምክትል ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሞክበርን ዋቢ ያደረገው የፋርስ ኒውስ ዘገባ ቴህራን ‘የኃይል ደህንነትን ለማረጋገጥ’ በሻንጋይ የትብብር ድርጅት ቀጠናዊ የጋዝ ማዕከል የመገንባት ሃሳብ እንዳላት መግለጿን አስነብቧል።

ኢራን ከቀጠናው አባል ሀገራት ጋር በመሆን ቀጠናዊ የጋዝ ማዕከል በማቋቋም አካባቢያዊ ትብብርን ለማጠናከር እና በዓለም አቀፉ የኃይል ገበያ ያላትን ተሳትፎ ማሳደግ እንደምትፈልግም ነው የገለጹት።

በሻንጋይ የትብብር ድርጅት የመሪዎች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የቴህራን እርምጃ አባል ሀገራቱ የኃይል ንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ምክት ፕሬዚዳንቱ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቴህራን ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ፈንድ ለማመንጨት ሃሳብ እንዳላትም ነው ያነሱት።

አያይዘውም ሀገራቸው የምህንድስና አገልግሎት ለማቅረብ እና ለነዳጅ፣ ጋዝ እና ፔትሮኬሚካል ዘርፎች የሚውሉ መሳሪያዎችን ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

ኢራን ምንም እንኳን በነዳጅ ምርቷ ላይ በአሜሪካ ማዕቀብ ቢጣልባትም ከፍተኛ ድፍድፍ ነዳጅና ጋዝ አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንደኛዋ ናት።

በሻንጋይ የትብብር ድርጅት ለማቋቋም ያሰበችው ቀጠናዊ የጋዝ ማዕከልም የአካባቢውን ሀገራት የኃይል ንግድ ልውውጥ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል መባሉን አር ቲ በዘገባው አመላክቷል።

በፈረንጆቹ 1990ዎች የተመሰረተው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት ኢራንን ጨምሮ ቻይና፣ ካዛክስታን፣ ኪርጊስታን፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ኡዝቤኪስታን እና ታጂኪስታንን በአባልነት ያካተተ እና ሌሎች ተጨማሪ ሀገራትን በታዛቢነት እና በልዩ አባልነት ያቀፈ ስብስብ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.