ተመድ የዓለም አቀፉን ሁኔታ ከግምት ያስገባ ማሻሻያ እንዲያደርግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቻርተር ላይ ተወያይቶ የዓለም አቀፉን ሁኔታ ከግምት ያስገባ ማሻሻያ እንዲያደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ አዲስ አበባ በሚገኘው አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደው 78ኛው የተመድ መታሰቢያ ቀን መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡
አምባሳደር ምሥጋኑ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ መሥራች አባል እንደመሆኗ የተመድን የቻርተር መርኅዎች ትደግፋለች ብለዋል።
በተመድ ውስጥ የባለ-ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ድምጽ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተመድ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን አጋርነት እንዲሁም ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አሥምረውበታል።
በመርሐ-ግብሩ የተመድ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች መገኘታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ ያመላክታል፡፡