Fana: At a Speed of Life!

24 ሰዓት በተደረገው 3 ሺህ 271 የላብራቶሪ ምርመራ በ14 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3 ሺህ 271 የላብራቶሪ ምርመራ በ14 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 365 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቅዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ እድሜያቸው ከ9 እስከ 68 ዓመት የሆኑ 11 ወንዶችና 3 ሴቶች ናቸው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 9 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም መካከል 1 ሰው የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ፣ 7 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 1 ሰው ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ አምስት ሰዎች ደግሞ 1 ሰው በትግራይ ክልል (የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ፤ በመቐለ ለይቶ ማቆያ ያለ) 1 ሰው በኦሮሚያ ክልል (የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ) እንዲሁም 3 ሰዎች በሶማሌ ክልል (ጅግጅጋ ልይቶ ማቆያ) ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በትናንትናው እለት በወጣው ሪፖርት ላይ ከአማራ ክልል (ሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማ ለይቶ ማቆያ) ተብሎ የተገለፀው ግንቦት 9 በወጣው ሪፖርት ላይ ተገልፆ የነበረ እና ትናንት በድጋሚ ሪፖርት መደረጉን በመግለፅ፤ በትናንትናው እለት ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 34 መሆኑን ሚኒስቴሩ ከይቅርታ ጋር ገልጿል።

በሌላ በኩል በትናንትናው እለት 3 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 1 ሰው ደግሞ ከአፋር ክልል በድምሩ 4 ተጨማሪ ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸውንና በአጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 120 መድረሱንም አስታውቀዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ62 ሺህ 300 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 365 ደርሷል።

አሁን ላይ 238 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ እስካሁንም 120 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል፤ የ5 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን መመለሳቸው ይታወሳል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.