ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡
ሥምምነቱን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የኮሪያ የኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ማሻሻያ ተቋም ፕሬዚዳንት ብዬንግ ጁ ሚን (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን የደቡብ ኮሪያ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
የኮሪያ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ማሻሻያ ተቋም ፕሬዘዳንት ብዬንግ ጁ ሚን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገራቸው የግብርና ሜካናይዜሽን ላይ ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ ግብርናን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋፀዖ እንደሚያደርግ ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል፡፡
በደቡብ ኮሪያ የሚደረገው የግብርና ሜካናይዜሽን ድጋፍ ÷ የግብርና ማሽነሪዎች ልማትና ጥገና፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ አግሮ ፕሮሰሲንግና የስንዴ ልማትን በሜካናይዜሽን ከምርት እስከ ማቀነባበር ያካተተ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ስምምነቱ የዕሴት ሰንሰለትን የአሰራር ጥራት ለማዘመን የሚያግዝ መሆኑ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መገለጹን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ÷ የመግባቢያ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ስምምነቱ የንግድ ስራን ዲጂታል ለማድረግ፣ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም በንግድ ዘርፍ ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ባንግ ሙን ኬዮ በበኩላቸው÷ ስምምነቱ የሁለትዮሽ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚያስችል ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡