ከአሸባሪ መረጃዎች ሥርጭት ጋር በተያያዘ ኅብረቱ “ኤክስ” ላይ ምርመራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት ቀደም ሲል ትዊተር በመባል ይታወቅ የነበረው የአሁኑ “ኤክስ” ላይ የሽብር ይዘት ካላቸው መረጃዎች ስርጭት ጋር በተያያዘ ምርመራ ማካሄድ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ኅብረቱ “ኤክስ” ላይ ምርመራ የጀመረው ከጥላቻ ንግግር፣ ከሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እንዲሁም ሌሎች ሕገ-ወጥ ይዘት ካላቸው መረጃዎች ሥርጭት ጋር በተያያዘ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡
በዚህ ሣምንት ኤክስ የማኅበራዊ ትሥሥር ገፅ ባለቤት ኤሎን መስክ በተጻፈ ደብዳቤ በሚሰራጩ መረጃዎች ላይ ክትትል የማያደርግ ከሆነ ቅጣት እንደሚጠብቀው ማስጠንቀቂያ ደርሶታል ተብሏል።
የኅብረቱ መግለጫ ከሐሰተኛ መረጃዎች ጋር በተያያዘ በኤክስ በኩል በእስራዔል-ጋዛ ጦርነት ላይ በተሰራጩ መረጃዎች ጉዳይ ምንም አላለም፡፡
አንድ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነር ግን ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ላይ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተዛባ መረጃ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያው ድርጅት ከኅብረቱ ጋር ተሥማምቶ ለመቀጠል የኅብረቱን የበይነ-መረብ ደንብና ሕግ አክብሮ ይንቀሳቀሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡
በአውሮፓ ኅብረት ሕግ መሠረት ድረ-ገፆችና ሌሎች ተዛማጅ የመረጃ መረብ አገልግሎቶች የኅብረቱን ሕግ የማያከብሩ ከሆነ ከሚያገኙት ትርፍ እስከ 6 በመቶ ድረስ ቅጣት ይጣልባቸዋል።