Fana: At a Speed of Life!

በመስከረም ወር የተከበሩ በዓላት እንዲታወኩ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም፤ ሕዝቡ በፍቅርና በሰላም በዓላቱን አክብሯል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመስከረም ወር የተከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በተለያዩ አካላት እንዲታወኩ ከፍተኛ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅርና በሰላም አንድነቱን አፅንቶ በዓላቱን አክብሯል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ የበዓላቱ በሰላም መከበር የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ ለሚሰሩት አካላት የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንግዜም ፍላጎት ሰላምና አንድነት መሆኑን አስተምሯል ብሏል።
በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ርብርብ ላደረጉ የፀጥታ አካላት፣ በየደረጃው ላሉ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮችና በተለይ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና አቅርቧል፡፡
በቀጣይ በሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላትም ሆነ በዕለታዊ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የጀመሩትን ተናብቦ ለሰላም ዘብ የመሆን አቋም አጠናክረው እንዲቀጥሉም ተጠይቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሕዝባዊ በዓላት ለሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት!
በመስከረም ወር የተከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ኹሉ እሴታቸውን ጠብቀው፣ ሀገራዊ አንድነትን አንፀባርቀውና ሰላምን ሰብከው ተጠናቅቀዋል፡፡
የመስቀል በዓል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከበሩት ጊፋታ፣ ያሆዴ፣ ዮ ማስቃላ፣ የቤኔ ሻዴዬ ባሮ፣ ቶኪ በአ፣ እና ሌሎችም የዘመን መለወጫ በዓላት በደማቅ ሁኔታ ተከብረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከበረው ሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዲ በዓልም እጅግ ውብ በኾነ ባህላዊ መንገድ ተከብሮ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓለም ሌላው በመስከረም ወር የተከበረ ታላቅ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓል ነው፡፡
እነዚህ በዓላት እንደወትሮው ኹሉ እፁብ ድንቅ በኾኑ ባህላዊ አልባሳት፣ ዝማሬዎች፣ ምግቦች እና ሁነቶች ደምቀው መከበራቸው ብቻ ሳይኾን ለሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት ተጨማሪ ኃይል ኾነው መጠናቀቃቸውም ያለው ሀገራዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
በእነዚህ በዓላት ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች በነቂስ ወጥቶ ታድሟል፡፡ የውጭ ቱሪስቶችም በበዓላቱ ላይ በብዛት ተሳትፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያላት እምቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የቱሪስት መስህብም ጎልቶ ታይቷል፡፡
በበዓላቱ ላይ የተሳተፉት ታዳሚዎችም በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠሩ የንግድ ልውውጦችን አከናውነዋል፡፡ በዓላቱን ለማድመቅ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብዓቶች፣ የትራንስፖርት ክፍያዎች፣ የምግብና የመጠጥ ሽያጮች፣ የፋሽንና ዲዛይን ሁነቶች፣ ኮንፈረንሶች፣ የአደባባይ ግብይቶች ወዘተ በበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ሲከናወኑ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡
በበዓላቱ ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ሥፍራ በብዙ ቁጥር በመገኘት ሀገራዊ አንድነቱን አሳይቷል፤ ፍቅር ተለዋውጧል፣ ፈጣሪውን በአንድነት አመስግኗል፣ ባህልና ማንነቱን በጋራ ገልጧል፤ በፍቅር ተጎራርሶ ከልብ ተመራርቋል፤ በሕብረት ዘምሮ በአብሮነት ስሜት ጨፍሯል፡፡
ከመኖሪያ ቀያቸው ርቀው ሄደው በዓላቱን ያከበሩ ሰዎችም በታላቅ የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት በኹሉም አካባቢዎች በክብር ተስተናግደዋል፡፡ ይህ ኹሉ ሀገራዊ የአብሮነት ስሜትን ያጠናከረ ታላቅ ክስተት ነበር፡፡
በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ በአራቱም አቅጣጫ በተመሳሳይ ወቅት አንድነቱን ሲያፀና እና እርስበርሱ በአብሮነት ሲተሳሰር ያለ አንዳች ኮሽታ በፍፁም ሰላማዊ መንገድ መኾኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰላም ውጭ ምንም አጀንዳ እንደሌለው ዳግም በተግባር የታየበት ነው፡፡
መንግሥት እና ሕዝብ ለዘላቂ ሰላም በትብብር እያከናወኑት ያለው ተግባር ፍሬ ማፍራቱንም በእነዚህ በዓላት ላይ በግልፅ ተመስክሯል፡፡
በተለያዩ አካላት በዓላቱ እንዲታወኩ ከፍተኛ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም፤ ሰሚ ጆሮ አጥተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅርና በሰላም አንድነቱን አፅንቶ በዓላቱን በሰላም አክብሯል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ ለሚሰሩት አካላትም የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንግዜም ፍላጎት ሰላምና አንድነት መኾኑን አስተምሯል።
በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ርብርብ ያደረጉ የፀጥታ አካላት፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮችና በተለይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባዋል።
በቀጣይ በሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላትም ኾነ በዕለታዊ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የጀመሩትን ተናብቦ ለሰላም ዘብ የመኾን አቋም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.