Fana: At a Speed of Life!

ብቁ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዕምሮ ጤና ላይ የሚሰሩ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

በዓለም ለ32ኛ ጊዜ ታስቦ የሚውለው የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን “የአዕምሮ ጤና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ቁጥር እያደገ መምጣቱን ጠቁመው ፥ አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ ሆስፒታሎች ሕክምናውን እየሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና ሕክምና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው የገለጹት፡፡

ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ብቁና ተወዳዳሪ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት ከትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል።

የአዕምሮ ጤና ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መገለል መከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን በበኩላቸው÷ የአዕምሮ ጤና ቀንን አስቦ ከመዋል ባለፈ ዘላቂነት ያለውና የተቀናጀ የግንዛቤ የመፍጠር ስራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።

ከመሪ ቃሉ ጽንሰ ሀሳብ በመነሳትም የአዕምሮ ጤና የሰብዓዊ መብት መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ ም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.