Fana: At a Speed of Life!

የዝንጅብል የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዝንጅብል በጥሬው ፣በሻይ፣በጭማቂ መልክና እንደ ምግብ ማጣፈጫ ቅመምነት ያገለግላል፡፡

ዝንጅብል በተለያየ መንገድ ለምግብነት ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም የተሻለ የጤና ጥቅም የሚኖረው በጥሬው መመገብ እንደሆነ ጥናቶች ያስረዳሉ ፡፡

ዝንጅብል ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ቫይታሚን ሲ፣ ማግኒዚየም እና ፖታሺየም እንዲሁም ‘ጅንጅሮል’ የተባለ ለመድሃኒትነት የሚውል እጅግ ጠቃሚ ተፈጥሯዊ ቅባት በውስጡ ይዟል፡፡

ይህ ተፈጥሯዊ ቅባት እብጠትን የመቀነስና አንቲኦክሲዳንት ሆኖ ከማገልገል በተጨማሪ በርካታ ሌሎች የጤና ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡

ዝንጅብል “ኦስቲዮአርትራይተስ” የተባለ በአዛውንቶች ላይ የሚከሰት የመገጣጠሚያ ህመምን ለማስታገስ ፣በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ቁርጠትን ለማስታገስ ፣የደምና የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር፣የሆድ ህመምን እንዲሁም በእርግዝና ጊዜና በሌሎች ምክንያቶች የሚመጣ የማቅለሽለሽና የማስመለስ ችግርን ለማስታገስ ይረዳል፡፡

በተጨማሪም÷ ዝንጅብልን በተለያዩ የአመጋገብ ዘዴዎች መጠቀም የምግብ ልመትን ማፋጠን ፣በልብ ህመም የመጠቃት ሁኔታን መቀነስ፣የቆዳ ጤንነትን መጠበቅ፣ከመጠን ያለፈ ክብደትን ለመቀነስና ሌሎች የጤና በረከቶች እንዳሉት የ ዩሲኤልኤ ኸልዝ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዝንጅብልን በጥሬው፣ በዱቄት፣ በዘይት ወይም በጭማቂ መልክ መጠቀም የሚቻል ቢሆንም በጥሬው መመገብ ግን የተሸለ የ‘ጅንጅሮል’ መጠን ስለሚኖረው የተሻለ እንደሆነ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በተጨማሪም ÷ ዝንጅብል የተሻለ የጤና ጠቀሜታ እንዲኖረው ከሦስት ሳምንታት በላይ ማቀዝቀዣ ውስጥ መቆየት እንደሌለበትም ይመከራል፡፡

ዝንጅብልን በየቀኑ መጠቀም የሚመከር ቢሆንም በቀን ውስጥ መጠቀም የሚገባው የዝንጅብል መጠን ግን ከሦስት እስከ አራት ግራም መብለጥ እንደሌለበት የሥነ- አመጋገብ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ሆኖም ግን ለነፍሰ ጡር እናት ከአንድ ግራም በላይ ዝንጅብል መውሰድ የሚመከር አይሆንም ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

በቀን ከሥድስት ግራም በላይ ዝንጅብል መውሰድ የጨጓራ ህመም፣ ቃር እና ተቅማጥ የመሳሰሉ ችግሮችን እንደሚያስከትልም ይገልጻሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.