በእስራዔል – ጋዛ ጦርነት እስከ አሁን ከ1 ሺህ 600 በላይ ሕይወት መቀጠፉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራዔል ወታደራዊ ኃይል ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር በገባበት ጦርነት ከ1 ሺህ 600 በላይ ሕይወት መቀጠፉ ተገለጸ፡፡
በጦርነቱ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 704ቱ ፍልስጤማውያን ሲሆኑ ከ900 የሚልቁት ደግሞ እስራዔላውያን መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ÷ በእስራዔል ጦር ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ ጋዛ ሆስፒታል የማደርስበት ከ”ጥቃት ነፃ ቀጠና” ይፈቀድልኝ እያለ ነው፡፡
በሌላ በኩል የእስራዔል ጦር ኃይል ሌሊቱን ጨምሮ የጋዛን ሰርጥ መደብደቡን ቀጥሏል፡፡
እስራዔል ጋዛን በሙሉ ኃይሏ መደብደብ የጀመረችው ጦርነት ተከፍቶብኛል ወደ ጦርነት መግባቴን እወቁልኝ ካለች በኋላ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ከመግለጫዋ በኋላ ምንም ዓይነት ምግብም ሆነ የነዳጅ አቅርቦት ወደ ፍልስጤም እንዳይገባ ማገዷም ተሰምቷል፡፡
በጀመረችው ጥቃትም ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።