ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በሚቻለው ሁሉ ኢትዮጵያን እንደሚደግፍ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ኢትዮጵያን ከፍልሰት ጋር በተገናኙ ጉዳዮች በሚቻለው ሁሉ እንደሚደግፍ አስታወቀ፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተሥፋዬ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አዲሷ ተሿሚ ዋና ዳይሬክተር አሚ ኢ. ፖፕ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር÷ ሥደተኞችን መልሶ በማደራጀት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በተለያዩ የማኅበራዊ ጥበቃ ሥራዎች የበኩሉን ለመወጣትና የፍልሰተኞችን ፈተናዎች ለማቃለል ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።
በውይይታቸው ወቅት ኤርጎጌ ተሥፋዬ (ዶ/ር) ከዋና ዳይሬክተሯ ጋር በፍልሰተኞች ጉዳይ ላይ፣ ከፍልሰት ተመላሾች በሚገኙበት ሁኔታ እንዲሁም ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ፍልሰተኞች ላይ የሚደርሰውን በደል ለመከላከል ሊደረጉ ስለሚገባቸው ድጋፎች መክረዋል።
ሚኒስትሯ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት÷ ከፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ ለተመለሱ ማኅበራዊና የሥነ-ልቦና አገልግሎት በመሥጠት ረገድ ላበረከተው አስተዋፅዖና ለሌሎች በርካታ ድጋፎቹ አመስግነዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይም ከፍልሰት ተመላሾችን ለይቶ ለመመዝገብና በመረጃ ቋት ለማደራጀት የሚያስችል ሥርዓት ለማጠናከር፣ የጥሪ ማዕከል ለማቋቋም፣ ስለ ፍልሰት አስከፊነት ማኅብረተሰቡን ለማሳወቅ እንዲቻል የአየር ሰዓት ለመግዛት በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩ ከሌሎች አጋር አካላት ጋርም በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አሚ ፖፕ በበኩላቸው÷ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ጥበቃ አገልግሎትና በሴቶች ጉዳይ ላይ እየሠራ ያለውን ስራ አድንቀዋል።
በተለይ ለሴቶች የሰጠው ትኩረትና በጉዳዩ ላይ የሚፈጽመው ተግባር እንዳስደሰታቸው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡