Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል የተጠረጠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል የተጠረጠሩት የፀሀይ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስኪጅን ጨምሮ በ9 የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜን ለዐቃቤ ህግ የፈቀደው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ክስ መመስረቻ የተጠየቀባቸው የፀሀይ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ ኪያ ዦንግን ጨምሮ ዘጠኝ የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው።

ከዚህ በፊት በነበሩ ጊዜ ቀጠሮዎች ላይ ተጠርጣሪዎቹ በርካታ መጠን ያለው ዩሮ፣ የአሜሪካ ዶላርና የሌሎች ሀገራት ገንዘቦች በማተም ጥቁር ገበያን በማስፋፋት መጠርጠራቸው ተገልጾ ነበር።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተለያዩ የውጭ ሀገር ገንዘብ የሚታተምባቸው ማተሚያ ማሽኖች እና ለግብዓት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች መያዛቸውን ገልጾ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ማስታወቁ ይታወሳል።

በዛሬው ቀጠሮም የምርመራ ስራውን ማጠናቀቁ እና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ለተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በችሎት በመሰየም የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ገልጿል።

የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ÷ደንበኞቻቸው ተጨማሪ ጊዜ በእስር ማሳለፍ እንደሌለባቸው ጠቁመው የዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ ጥያቄን ተቃውመው ተከራክረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ክስ የመመስረቻ ጊዜ መሰጠት እንዳለበት በማመን ለዐቃቤ ህግ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.