በእስራዔል-ሃማስ ጦርነት በትንሹ የ1 ሺህ 113 ሰዎች ሕይወት መቀጠፉ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍልስጤሙ ሃማስና በእስራዔል መካከል የሚካሄደው ውጊያ እስካሁን ቢያንስ የ1 ሺህ 113 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ተገለጸ፡፡
ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 413ቱ ፍልስጤማውያን ሲሆኑ 700ዎቹ ደግሞ እስራዔላውያን ናቸው ተብሏል፡፡
የሃማስ ቡድን ከ130 በላይ ምርኮኞችን በጋዛ ማገቱን እወቁልኝ ብሏል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ እስራዔል 100 ሺህ የሚጠጉ ተጠባባቂ ወታደሮቿን በጋዛ አቅራቢያ አስፍራለች፡፡
በሃማስ ታጣቂዎችና በእስራዔል ወታደራዊ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ፍልሚያ በደቡባዊ እስራዔል ሦስት ሥፍራዎች ተፋፍሞ እንደቀጠለ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ሥፍራዎቹ የካርሚያዋ ኪቡዝ፣ አሽኬሎን እና ስዴሮት ከተሞች መሆናቸው ሲነገር በአካባቢዎቹ ከባድ ውጊያ እየተሰማ መሆኑ ተነግሯል።
በእስራዔልና በፍልስጤሙ ሃማስ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ወደ ሙሉ ውጊያ ከተቀየረ ሁለተኛ ቀኑን ደፍኗል፡፡