Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 2ሺህ 742 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 2ሺህ 742 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ማህበር ምስረታ መድረክ በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ የቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ 2 ሺህ 742 ቶን የታጠበ እና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም ህገወጥ የቡና ምርት ዝውውርና ግብይትን ለመከላከል ፣ ቀልጣፋ የብድር አገልግሎት እንዲኖርና ብልሹ አሰራሮችን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በተሰራው ዘርፈ ብዙ ሥራ ዝቅተኛ የነበረውን የቡና መሬት ሽፋን ወደ 147ሺህ 347 ሄክታር ማድረስ መቻሉንም ነው የተናገሩት፡፡

በቡና ላይ የባለቤትነት ጥያቄዎችን የሚፈጥሩ ማነቆዎችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ÷ ለቡናው ዘርፍ እንደ ሀገር መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የታቀደውን የቡና ማህበር አደረጃጀት በየደረጃው በማዋቀር ከባለድርሻ ላጋር በቅንጅት መስራት አስፈለጊ መሆኑንም ነው ያበብራሩት።

የብሔራዊ ቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት ÷ ማህበሩ በዋናነት ቡና አምራቾች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶች ለመፍታት ይሰራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.