Fana: At a Speed of Life!

ትኩረት መነፈግና ተጽዕኖው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰዎችን ትኩረት ማጣት ጭንቀትና ከፍተኛ የሆነ ድባቴ እንዲሁም ከፍተኛ የጤና ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የህክምና ሊቆች ይናገራሉ፡፡

የተቀናጀ የአዕምሮ ጤና ስፔሻሊስት አበበ አምባው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ትኩረት መነፈግ በሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ጫናን አስመልክተው ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም ፥ ሰዎች በተለይም ህጻናት ከሚገባው በታች ትኩረት ሲያገኙ የወደፊት ህይዎታቸው ላይ ተጽእኖ ሊያደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

አንድ ሰው የሚገባውን ያህል ትኩረት ካላገኘ ምንም ያሕል አቅም ቢኖረውም እንኳን አቅሙን አውጥቶ ሊጠቀምበት የሚችልበት ዕድል አናሳ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

ግለሰቡ ‘’ሰው አይቀበለኝም ፤ ልክ ላልሆን እችላለሁ’’ ብሎ ስለሚያስብ ያለውን አቅም ለሕብረተሰቡ ሳያንጸበርቅ ሊቀር ይችላልም ብለዋል፡፡

ከሰው መሸሽ፣ ለራስ ዝቅተኛ የሆነ ስሜት መኖር፣ ከፍተኛ የሆነ የእንቅልፍ ማብዛት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ሊመጡ ይችላሉም ነው ያሉት የህክምና ባለሙያው፡፡

ይህን ተከትሎም ሕመሙ ሲባባስ ሕክምና ሊያስፈልገው እ ንደሚችል መገንዘብ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ይህ ጉዳይም አብዛኛውን ጊዜ ችላ እንደሚባል ያነሱት የአዕምሮ ጤና ስፔሻሊስቱ ፥ ‘’አመሏ/ሉ ነው ፤ ብቻው/ዋን መሆን ትወዳለች/ይወዳል’’ በማለት የተለያዩ ስሞች እንደሚሰጡም ነው ያብራሩት፡፡

ይህም ሣይታወቅ ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ችግር ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል ማወቅ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ፡፡

መፍትሄውም ፥ ከቤተሰብ ጋር ማውራትና ችግሮችን መፍታት፣ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሃሳብ መለዋወጥ ካለባቸው ድባቴ ወይንም ጥሩ ያልሆነ ስሜት እንዲወጡ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.