አሜሪካ በ42 የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለሩሲያ ወታደራዊ ኃይል “የጦር ቁሶችን አቅርበዋል” ባለቻቸው 42 የቻይና ኩባንያዎች ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ገድብ መጣሏን አስታወቀች፡፡
በተጨማሪም በኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ ሕንድ፣ ቱርክ፣ እንግሊዝ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የሚመሩ ኩባንያዎች ላይ የውጭ ንግድ ቁጥጥር ገድብ መጣሉን የአሜሪካ ንግድ ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ ለሚያካሂደው ጦርነት ድጋፍ በሚያደርጉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይልም ነው ዲፓርትመንቱ ያስታወቀው፡፡
የአሜሪካ ምርቶችን ወደ ሩሲያ መከላከያ ኢንዱስትሪ የሚልኩ ኩባንያዎችን ለመለየት ከተለያዩ ሀገራት እና አጋር ድርጅቶች ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም ነው የገለጸው፡፡
አሜሪካ በቻይና ኩባንያዎች የጣለችው የወጪ ንግድ ገድብ አሜሪካ የምታመርታቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለሩሲያ ወታደራዊ ኃይል እንዳይተላለፍ የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ዒላማቸውን እንዲመቱ ለማድረግ ያግዛሉ የተባሉት የማይክሮ ኤሌክትሮኒክ ስርዓቶች አሜሪካ ለሩሲያ ጦር እንዲደርስ ከማትፈልጋቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል መሆናቸውንጠቅሶ አር ቲ ዘግቧል፡፡