Fana: At a Speed of Life!

አቶ ፍቃዱ ተሰማ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሠላም እንዲከበር ያደረጉ አካላትን አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል እሴቱንና ውበቱን ጠብቆ በሠላም እንዲከበር ያደረጉ አካላትን አመሰገኑ፡፡

አቶ ፍቃዱ የሆረ ፊንፊኔ በዓል በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ ባስተላለፉት የምስጋና መልዕክት÷ የዘንድሮው ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ መከበሩን ገልጸዋል፡፡

ኢሬቻ የአንድነትና የወንድማማችነት መገለጫ ምልክት መሆኑንም በመልዕክታቸው አንስተዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“የምስጋና መልዕክት”

የዘንድሮው የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የኦሮሞን ሕዝብ ታላቅነት ከማረጋገጡም ሁኔታ እሴቱንና ውበቱን ጠብቆ በሠላማዊ መንገድ እንዲከበር የበኩላችሁን ድርሻ ለተወጣችሁ አካላት በሙሉ ያለኝን ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ።

የጠንካራ ባህል እና እሴት ባለቤት የሆንከው የኦሮሞ ሕዝብ የማንነትህ መገለጫ የሆነውን የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ከሌላው ወንድም ሕዝብ ጋር እውነተኛ መተሳሰብ፣ ፍቅር እና አንድነትን ባጠናከረ መልኩ ተከብሮ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ደስ አለን እላለሁ።

የዘንድሮው ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ በተለየ መልኩ በሚሊየኖች የሚቆጠረው የኦሮሞ ሕዝብ የተሳተፉበት፤ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎችም በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባሕላቸውን በሚያንፀባርቁ አልባሳቶቻቸው ደምቀውና ተውበው የተሰባሰቡበት፤ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችም በብዛት የተካፈሉበት ደማቅ በዓል መሆን ችለዋል።

ኢሬቻ የአንድነትና የወንድማማችነት መገለጫ ምልክት በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለ አንዳች ልዩነት የማንነታችሁ መገለጫ በሆነው ህብረ ቀለማት ተውባችሁ፤ ታላቅነታችሁን በሚመጥን ስነ ምግባርና ጨዋነት በዓሉን በሆራ ፊንፊኔ እንዲከበር በማድረጋችሁና በአቃፊነት የተዋበውን ታላቅነታችሁንም በማሳየታችሁ ምስጋና ይገባቹዋል።

ኢሬቻ ሠላም እና ፍቅር፤ ወንድማማችነትና አንድነታችንን የምናጠናክርበት በዓል በመሆኑ ከፈጣሪ ምህረትንና ቸርነትን ለተማፀናችሁልንና ስኬትን ላጎናጸፋችሁን አባ ገዳዎች እና ሐዳ ሲንቄዎች የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በየደረጃው የምትገኙ የፀጥታ አካላት በፀሐይና ብርድ ሳትበገሩ፤ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ያለ አንዳች መዘናጋት ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የአንድነት መገለጫ አይነተኛ ምልክት ሆኖ እንዲከበር ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

የኦሮሞ ቄሮና ቀሬ፤ በአንድ በኩል በኦሮሞ ሕዝብ ሕበረ ቀለማዊ አልባሳት በማጌጥ የቱሪዝም ሀብታችንን ለአለም በማስተዋወቅ በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ ውድቀትና ውርደት የሚናፍቁ ጠላቶቻችን አንዳች ክፍተት እንዳያገኙ በማድረግ ኢሬቻ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ደጀን በመሆን የሚጠበቅባችሁን ድርሻ በመወጣታችሁ ምስጋናችሁ እጥፍ ድርብ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጥ እፈልጋለሁ።

ሁሉም የሚዲያ ተቋማት፤ ከኢሬቻ መባቻ ጊዜ አንስቶ የበዓሉን ዕሴቶች፤ ምንነትና ክብር የአለም ሕዝብ እንዲገነዘበው ከማድረግ ጀምሮ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ረገድ ያበረከታችሁት አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነው።

ኢሬቻ የአንድነትና የወንድማማችነት ምልክት፤ የቱሪዝም ምንጭ መሆኑንና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በጋራ ወጥቶ የሚያከብር ታላቅ በዓል መሆኑን ዓለም እንዲገነዘበው ከማድረግም ባሻገር በዓሉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ዕሴቱን ጠብቆ እንዲከናወን ላበረከታችሁት አስተዋፅዖ ያለኝ ምስጋና ላቅ ያለ ነው።

አትዮጵያዊ አንድነታችን የአብሮነታችን ምንጭ፣ የውበታችን መገለጫ መሆኑን በመረዳት በባሕላዊ አልባሳት ተውባችሁና ደምቃችሁ ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት ለሆናችሁ ወንድምና እህት ብሔር ብሔረሰቦች እና አጋርነታችሁን ላሳያችሁ የበዓሉ ታዳሚዎች ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ።

የፊንፊኔ ከተማ አስተዳደርና የከተማዋ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ የገቡትን እንግዶች ተቀብላችሁ በማስተናገድ እና ለኦሮሞ ሕዝብ ያላችሁን ትልቅ አክብሮት አሳይታቹሃልና እናመሰግናለን።

በአጠቃላይ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ዕሴቱን ጠብቆ በሠላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከጅምሩ አንስቶ እስከ በዓሉ ፍፃሜ ድረስ የበኩላችሁን ድርሻ የተወጣችሁ አካላት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፤ በነገው ዕለትም በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆራ ሀርሰዲ በዓል በተመሳሳይ መልኩ የተሳካ እንዲሆን በተለመደው ቁርጠኝነት ሚናችሁን እንድትወጡ አደራ ማለት እወዳለሁ።

አመሰግናለሁ!

ፍቃዱ ተሰማ

የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.