እስራዔል እና ፍልስጤም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ሩሲያ ጠየቀች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራዔል እና ፍልስጤም ጦር መማዘዙን አቁመው ውዝግባቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ሩሲያ ጠየቀች፡፡
የሩሲያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካዒል ቦግዳኖቭ÷ “የተፈጠረው ውጥረት መቋጫ ወደ ሌለው ግጭት እንዳያመራ ሀገራቱ በንግግር ችግሮቻቸውን ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል፡፡
ሩሲያ የሁለቱን ወገኖች ጥቅም ባማከለ ሁኔታ ችግሮቻቸው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እንደምትፈልግ ገልጸው÷ ለዚህም የሚጠበቅባትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ናት ማለታቸውን ስፑትኒክ ዘግቧል፡፡
ሀገራቸው ከእስራዔል፣ ፍልስጤም፣ ግብፅ እና ሌሎች ዓረብ ሀገራት ጋር በመሆን ጉዳዩን ለማረጋጋት እየጣረች መሆኗንም አመላክተዋል፡፡
በተፈጠረው ግጭት እስካሁን በርካቶች መጎዳታቸውን እና በንብረት ላይም ውድመት መድረሱን ጠቁመው÷ ሁለቱ ወገኖች የገቡበት ግጭት ወደ ተባባሰ ሁኔታ ሳይገባ በአስቸኳይ ግጭቱን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ፍልሥጤም በእስራዔል ላይ ቅፅበታዊ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን በይፋ አስታውቀዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች ከፍልስጤም መተኮሳቸውን ተከትሎ እስራዔል በዓየር ድብደባ የታገዘ አጸፋ መውሰዷን አልጀዚራ ዘግቧል፡