ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት የጋራ መርህ ላይ ተመስርተው ጠንካራ ተቋም እንዲፈጥሩ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት የጋራ መርህ ላይ ተመስርተው ጠንካራ ተቋም እንዲፈጥሩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና ከኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል የእምነት መሪዎች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የጋራ እሴቶችን በመጠቀም ፈጣሪን የሚፈራ፣ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ትውልድ መፍጠር ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህንንም የሚያስችል ዘመን የሚሻገር ተቋም የኃይማኖት ተቋማቱ እንዲፈጥሩም ነው ያሳሰቡት።
ኢትዮጵያ በሁሉም እምነት ውስጥ በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ እውቀት የዳበሩ፣ በታሪክ እና በእድሜ የበሰሉ መሪዎች ቢኖሯትም ጠንካራ ተቋም ባለመኖሩ በአግባቡ እንዳልተጠቀመች አንስተዋል።
የሚፈጠረው ተቋምም ዋነኛ ዓላማው ሀገራዊ ሀብትን በትክክል አውቆና አቅምን አሰባስቦ ሀገር እንድትጠቀም ማስቻል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ ድምፅ ለሌላቸው ሰዎች ድምፅ የሚሆን፣ በሰላም ግንባታ ላይ የሚሳተፍ ፣ በአደጋ ጊዜ ተባብሮ የሚሰራ እና የህዝቡን ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ የሚተጋ እና የማገልገል ልምድን ለወጣቱ የሚያስተላልፍ ይሆናልም ብለዋል።
የኃይማኖት መሪዎቹ ጠንካራ ተቋም መመስረቱ ላይ በመስማማት በቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።
በአልአዛር ታደለ