Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል ደመራና የመውሊድ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ዝግጅት ማድረጉን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራና የመውሊድ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለጸ፡፡

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፤ ለመስቀል ደመራና ለመውሊድ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።

ሁለቱም በዓላት ሀይማኖታዊ ሥርዓታቸው በሚፈቅደው መሠረት በሰላም እንዲጠናቀቁ ከሃይማኖት አባቶችና ከሰላም ወዳዱ ኅብረተሰብ ጋር በመተባበር በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱንም ገልጿል።

በሃይማኖት ሽፋን እኩይ የፖለቲካ አጀንዳዎች ለማራመድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገቢ እንዳልሆኑ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓላቱ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ውጪ ግጭትና ሁከት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደማይቻል አስገንዝቧል፡፡

በባነር፣ በአልባሳት እንዲሁም ርችት የመሳሰሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን፣ ስለታማና የጦር መሳሪያ በማንኛውም ሁኔታ በዓላቱ ወደ ሚከበሩባቸው ቦታዎች ይዞ መግባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ገልጿል፡፡

ክልከላውን ተላልፈው የበዓላቱን ድባብ ለማደብዘዝ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አስታውቋል።

በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡም ለፀጥታ ኃይሉ አጋዥና ተባባሪ በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል።

በበዓላቱ ድባብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች፣ በዓሉን በኮሚቴነት የሚያስተባብሩና የሚመሩ አካላት፣ ሕዝበ ክርስቲያንና ሕዝበ ሙስሊሙ ከፀጥታ አካላት የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የበዓላቱ ታዳሚዎች የበዓላቱን ሥነ-ሥርዓት የሚያውክ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት፤ ሰላምና ደኅንነት የማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ ኅብረተሰቡ የጋራ ጥረቱንና አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል በመግለጫ ጠይቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.