Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል – የጋራ ግብረ-ኃይሉ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይሉ ሥነ-ምግባር ተላብሶ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በየደረጃው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡

የመስቀል ደመራ በዓልን በሰላም ለማክበር የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል እና የሀይማኖት አባቶች ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ÷ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ለፀጥታ ኃይሉ አመራሮችና አባላት ገለፃ ተሰጥቶ ለተልዕኮ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ማራገብና ማንፀባረቅ ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓል አከባበሩ ሥነ-ሥርዓት ውጭ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎች እና ማንኛውም ሁከት አነሳሽ ነገሮችን በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ ይዞ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ክልከላውን በሚተላለፉ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረው፤ ህብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መጠየቃቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ዋና ስራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው÷ ቤተክርስቲያኗ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ያደረገችውን ዝግጅት ገልጸዋል፡፡

ግብረ-ኃይሉ ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት ውጭ የበዓሉን ድባብ ለማደብዘዝ እና ክብሯን ለመንካት በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ከጎናቸው እንዲሆን የሃይማኖት አባቶቹ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.