የአየር ንብረት ለውጥ በሊቢያ የደረሰውን የጎርፍ አደጋ የከፋ እንዲሆን ማድረጉ በጥናት ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊቢያ ለደረሰው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ከሚጠቀሱ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ጥናት አመላከተ፡፡
ከየሀገራቱ ተሰባስበው የዓለምን የዓየር ንብረት በማጥናት መፍትሄ የሚያመላክቱት የሳይንቲስቶች ቡድን በዛሬው ዕለት ግኝታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
እንደ ኤቢሲ ኒውስ ዘገባ በሳይንቲስቶቹ ግኝት መሠረት በሊቢያ የበርካቶችን ሕይወት ለቀጠፈው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ምክንያቱ የከባቢ አየር ንብረት ሁኔታ መዛባት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ለአየር ንብረት መዛባቱ ምክንያት የሆኑት የሰው ልጆች ባደረሱት ብክለት የአየር ንብረት እንዲቃወስና ከባድ ዝናብ እንዲጥል እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በግሪክ፣ በቡልጋሪያና ቱርክ የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ በ10 እጥፍ÷ እንዲሁም በሊቢያ ደግሞ በ50 እጥፍ የከፋ እንዲሆን ማድረጉን ሳይንቲስቶቹ በጥናት ውጤታቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡