ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲወያዩ ለማስቻል እየተሰራ ነው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲወያዩ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ።
የምክክር ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ዞንከጋምቤላ ከተማ አስተዳደርና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋምቤላ ከተማ እየመከረ ይገኛል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ኮሚሽኑ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው።
መድረኩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው ለሚሳተፉ ተወካዮች በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ባለፉት ጊዜያት የመወያየቱ እድል ስላልነበረ በግጭትና በጦርነት በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል ያሉት መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ከማጃንግ ዞን ሁለት ወረዳዎች እና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ እንዲሁም ከጋምቤላ ከተማ መስተዳድር 400 ያህል ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ከክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ደግሞ ከኑዌርና አኝዋክ ዞን የተመረጡ ተሳታፊዎች ጋር ውይይቱና የማህበረሰብ ተወካዮችን የመምረጥ ስራው እንደሚቀጥል ተገልጿል።