ባለፉት 4 አመታት የወጪ ንግድ ዘርፉ በአማካይ 7 በመቶ እድገት ማስመዝገቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት 4 አመታት የወጪ ንግድ ዘርፉ በአማካይ በ7 በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከውጭ ንግድ ዘርፎች ግብርና ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን የገለፀው ሚኒስቴሩ ÷በዋነኝነት ቡና ፣ የቅባት እህሎችና አበባ እንዲሁም ጫት ከፍተኛ የወጪ ንግድ ምርቶች ናቸው ብሏል፡፡
የቡና እና አበባ ምርቶችም ከታቀደው በላይ ትርፍ የታየባቸው የወጪ ንግድ ዘርፎች መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡
የማዕድን ምርት በወጪ ምርት እድገት ካሳዩ ዘርፎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በተለይም ወርቅ ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የማምረቻ ዘርፍ በወጪ ንግድ እድገት ሶስተኛ ደረጃ መያዙ የተገለፀ ሲሆን የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ለውጪ ገበያ እየቀረቡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በአገልግሎት ዘርፍ በ2012 ዓ.ም 4 ነጥብ 69 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ማግኘት መቻሉን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡