Fana: At a Speed of Life!

በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን – የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትውልድን በስነ-ምግባር በማነጽ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀን “ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የሃይማኖት አባቶች ትውልድን በስነ-ምግባር በማነጽ አገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሁሉም የትምህርት ተቋማት ሀገር ተረካቢ ትውልድን የማነጽ በጎ ሚናቸውን በኃላፊነት ስሜት ሊወጡ እንደሚገባም አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮርክና አካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ እንዳሉት÷ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ህጻናት በስነ-ምግባር ታንጸው መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ አበክራ እየሰራች ነው፡፡

ሀገር ወዳድ መልካም ዜጋን መፍጠር የመንግስት ስራ ብቻ ባለመሆኑ ቤተ-ክርስቲያኒቱ በጋራ እንደምትሰራ ገልጸው÷ትውልድን በማነጽና በመገንባት ረገድ የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ይወጣሉ ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሼህ ሁሴን በሽር በበኩላቸው÷ “ሀገር የትውልድ ድምር ውጤት ናት” ብለዋል፡፡

ትውልዱ ስርዓት አለብኝነትን እንዲጸየፍ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች መልካም ዜጋን ለሀገር ለማበርከት እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

በቤተ ክርስትያኗ አስተምህሮ ለትውልድ ግንባታ ቅድሚያ እንደሚሰጥ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የትምህርት ክፍል ኃላፊ አባ ዳንኤል ሃሶ ናቸው፡፡

አማኞች ልጆቻቸውን በስነ-ምግባር እንዲያሳድጉ ቤተ-ክርስቲያኗ አሰገዳጅ መመሪያ አላት ያሉት አባ ዳንኤል÷ምዕመናንም ትዕዛዙን በማክበር ለተፈጻሚነቱ ጥረት እንደሚያደርጉ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱሰ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው÷በእድሜ ደረጃ የተከፋፈለ የሰብዕና ግንባታ መንፈሳዊ ትምህርትን የማስተማር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችም የትውልድ ግንባታ ሚናቸውን ለማጠናከር የግብረ ገብ ትምህርት ላይ ማተኮር አለባቸው ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.