ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ከደቡብ ክልል የዞን አመራሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የዞን አመራሮች ጋር ተወያዩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ውይይቱን አስመልክተው በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክትም “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በብዙ የተፈጥሮ እና የባህል መስህቦች የታደለ ነው” ብለዋል።
እነዚህን መልካም ጎኖች ለመጠቀም በጋራ ከሠራን፣ ክልሉ ለሌሎች የሚተርፍ የልማት ማዕከል እንደሚሆን ለበርካታ ጊዜያት መናገራቸውንም አስታውሰዋል።
“ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ ወደ ክልሉ በተደጋጋሚ በመጓዝ ለማኅበረሰብ ልማት በእጅጉ ስለሚያስፈልጉ ጉዳዮች ከአንደበታቸው አድምጫለሁ፤ ሁሉንም መሠረታዊ ፍላጎቶች በአንድ ጊዜ ለማሟላት የሚቻል ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ዐበይት የመሠረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንት እና ተያያዥ ሥራዎች ተከናውነዋል” ሲሉም ገልፀዋል።
በዛሬው እለት ከክልሉ የዞን አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ በደቡብ ክልል ባለ ብዙ ገጽ ዕድገት እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የአስተዳደራዊ መዋቅር መርኆውን ቅድሚያ ሰጥቶ መመልከት አስፈላጊ እንደ ሆነ መስማማታቸውንም አስታውቅዋል።
በዚህ ውይይት፣ በዝርዝር ሊታዩ የሚገባቸው ሌሎች ጉዳዮችም ተነሥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ “ጉዳዮቹ የበለጠ ዳብረው ተመልሰን እንድንወያይባቸው ስምምነት ላይ ደርሰናል” ብለዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።