የአማራ ክልል አጋጥሞት ከነበረው የፀጥታ ስጋት በመውጣት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለስ መቻሉን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል አጋጥሞት ከነበረው የፀጥታ ስጋት በመውጣት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለስ መቻሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡
ወቅታዊ የአማራ ክልል ሁኔታን አስመልክቶ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በሰጡት መግለጫ÷ ክልሉ አጋጥሞት ከነበረው የፀጥታ ስጋት በመውጣት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለስ መቻሉን አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ህገመንግስታዊ ስርዓትን መናድና ክልሉን የማፍረስ ተልዕኮ ከሽፏል ያሉ ሲሆን ÷ሁሉንም ዞንና ወረዳዎችን ነፃ ማውጣት መቻሉንም ገልፀዋል።
ለዚህም የክልሉ ህዝብ፣የሀገርመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር ለከፈሉት መሥዋዕትነት ምስጋና አቅርበዋል።
ከፀጥታ ማስከበር ተግባራት ባለፈ የሠላም ግንባታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ አረጋ ከበደ በዚህም የህዝብ ጥያቄዎችና ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በሠላማዊ ሁኔታ ፣በህግ እና በድርድር መሆኑን ከማህበሰሠቡ ጋር መግባባት ላይ የተደረሰበት ስለመሆኑ አንስተዋል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ የተገኘውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ አስከ ላይኛው የመንግስት አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ የመልሶ ማደራጀት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በአጋጠመው የፀጥታ ችግር የመንግስት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መደበኛ የልማት ስራዎችን ከድህረ ግጭት ተግባራት ጋር ወደ ስራ ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።
ህብረተሠቡ የአካባቢው ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ያሳየውን ትጋት አጠናክሮ እንዲቀጥልና ለመደበኛ የመንግስት አገልግሎቶች መመለስ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።