የአገልጋይነት ቀን በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀን በአዲስ አበባ በተለያዩ ሁነቶች በመከበር ላይ ይገኛል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አለምፀሃይ ጳውሎስ በጋራ በመሆን የሃገር አቋራጭ አውቶቢስ አሽከርካሪዎችን እና በዘርፉ ላይ ያሉ አካላትን ስለአገልግሎታቸው አመስግነዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ያሉ አካላት ስለአገልግሎታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ በማሽከርከር ወገኖቻቸውን እንዲያገለግሉም ነው አደራ ያሉት።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የዛሬው ቀን የአገልጋይነት ቀን ሆኖ እንዲዘከር መንግስት ሲወስን በሁሉም ሴክተር ያሉ ቅን አገልጋዮች እንዲታወሱና እንዲመሰገኑ ነው ብለዋል፡፡
በትራንስፖርት ሴክተር የተሰማሩ አገልጋዮች ወዳጅና ዘመድን የሚያገናኙና ሁሉንም ያለልዩነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች ሲሉ ገልጸዋል።
አሽከርካሪዎች የኢኮኖሚም ደም ስር ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።