Fana: At a Speed of Life!

በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ የጋራ አቋም ያስፈልገናል – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ የጋራ አቋም ያስፈልገናል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በናይሮቢ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸው ጉባዔውን ላዘጋጀው የአፍሪካ ሕብረት እና ጉባዔውን እያስተናገደች ለምትገኘው ኬንያ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክታ ድምጿ ተሰሚነት እንዲያገኝ ጥረት ስታደርግ መቆየቷንም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ይህን ጥረት በማድረግ ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰው ፥ በዚህ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት ፎረም ላይ ጠንካራ የጋራ አቋም መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዛሬ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮረ ምክክር ቢሆንም የአህጉሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም ሰላም፣ ደህንነት እና ለውጥም የጋራ አቋማችንን ይሻሉም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፡፡

በአህጉራችን ፍትህ እና ከድህንት መላቀቅን አስመልክቶ የጋራ አቋም እና በተግባር የተደገፈ እንቅስቃሴ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ይህን ሁሉ ለማድረግ ግን በአፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩሽን ላይ ሀብት ማፍሰስ ማድረግ እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡

ኢትዮጵያ ያለፉት አስር ዓመታት ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የአንበጣ መንጋ መከሰት እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጡ አደጋዎች እንደተፈራረቁባት አንስተው ፥ በዚህም ብዙዎች ለጉዳት እንደተዳረጉም ነው የገለጹት፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ብዙ ቢሊየን ችግኞች በህዝቡ በጎ ፍቃድኝነት መተከሉን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ እንደሆነም ነው አክለው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ ፥ በዚህም በጉልህ የሚነሳው የስንዴ ምርት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ለዚህም እገዛ ያደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክን አመስግነዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.