ዳሸን ባንክ ከኢትዮጵያ ባንኮች የመጀመሪያ የሆነውን የ40 ሚሊየን ዶላር ብድር አገኘ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳሸን ባንክ ከኢትዮጵያ ባንኮች የመጀመሪያ የሆነውን የ40 ሚሊየን ዶላር ብድር ማግኘቱን ገለጸ፡፡
የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት (ቢ.አይ.አይ) እና የኔዘርላንድ የስራ ፈጠራና ልማት ባንክ (ኤፍ ኤም ኦ) ለባንኩ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ባንኩ ያገኘው ብድር ለወጪ ንግድ የሚሰጠውን ብድር ይበልጥ እንዲያጠናክር ያስችለዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ለውጭ ምንዛሪ የሚሰጠው ብድር የግብርና ምርት ላኪዎች አዳዲስ ማሽነሪዎችን በመግዛት የምርት ሂደታቸውን እንዲያዘምኑና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እንዲሁም የግብርና ምርት ላኪዎችን የገቢ አቅም በማሳደግ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
ቢ.አይ.አይ እና ኤፍ.ኤም.ኦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፈረንጆቹ 2021 አዲስ ባወጣው የውጭ ምንዛሪ ማቀላጠፊያ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ለሚገኝ የፋይናንስ ተቋም በውጭ ምንዛሪ የቀረበ የረዥም ጊዜ ብድር ሲሰጡ የመጀመሪያዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡
ይሄም ገበያውን በማነቃቃት ከዓለም አቀፍ መዋዕለ-ንዋይ አቅራቢዎች ተጨማሪ ሃብት ለማሰባሰብ መተማመንን ለመገንባት እንደሚያግዝ ባንኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ÷ ባንኩ ከሁለቱ የልማት አጋሮቹ ላገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቢ.አይ.አይ ዋና ስራ አስፈጻሚና የፋይናንሺያል አገልግሎት ኃላፊ ስቴፈን ፕሪስትሊ በበኩላቸው ÷ ባለፉት ዓመታት ቢ.አይ.አይ በኢትዮጵያ ቀዳሚ መዋዕለ-ንዋይ አፍሳሽ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡
የኤፍ.ኤም.ኦ የፋይናንሺያል ኢንስቲትዩሽን ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ማርኒክስ ሞንስፎርት ÷ አስፈላጊ የሆነውን በውጭምንዛሪ ብድር በውጪንግድ ላይ ያተኮረ ግብርና በመደገፍ ለሥራ ፈጠራና በገጠር አካባቢ የፋይናንስ አካታችነትን በማስፈን አስተዋጽኦ ለማድረግ ህልማችን ነው ብለዋል፡፡
ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ታላላቅ ባንኮች አንዱ ሲሆን ÷ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ ከ800 በላይ ቅርንጫፎቹ ከ5 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ያሉት ባንክ ነው።