አቡዳቢ ለ“ብሪክሱ” የጋራ ባንክ ካፒታል እንደምትለቅ ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የ“ብሪክስ” ሀገራት በጋራ ዕውን ላደረጉት “ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ” (ኤን.ዲ.ቢ) ተጨማሪ ካፒታል እንደምትለቅ ይፋ አደረገች፡፡
እንደ ሀገሪቷ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አብደላ ቢን ቱቅ አል ማርሪ ÷ አቡዳቢ አባልነቷን ተጠቅማ በቡድኑ ውስጥ ንግዷን ለማዳበርም እንደ ዕድል ትጠቀምበታለች ማለታቸውን አር ቲ ብሉምበርግን ዋቢ አድርጎ ፅፏል፡፡
አቡዳቢ በአማርኛ “አዲስ ልማት ባንክ” የሚል ትርጓሜ በሚይዘው “ኤን.ዲ.ቢ” የተሠኘ የቡድኑ ባንክ በመዋዕለ-ንዋይ መሳተፍ የጀመረችው ከዛሬ ሁለት ዓመታት ጀምሮ ነው፡፡
“ኤን.ዲ.ቢ” የተቋቋመው በፈረንጆቹ 2014 ሲሆን ፥ ያቋቋሙትም የመጀመሪያዎቹ የ”ብሪክስ” ቡድን መሥራች ሀገራት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡
የ”ብሪክሱ” (ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ) የተቋቋመው የቡድኑ አባል ሀገራትን በመሠረተ ልማት እና በሌሎች ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች በገንዘብ ለመደገፍ ነው።
ባንኩ በፈረንጆቹ 2015 መደበኛ የንግድ ሥራውን በይፋ ጀምሯል፡፡
አቡዳቢ (የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች) እጅግ ባለፀጋ ከሆኑ እና በነዳጅ ሐብት ከታደሉ ሀገራት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ነች፡፡
ምንም እንኳን ሚኒስትሩ ለብሪክሱ ባንክ ካፒታል እንደሚፈቅዱ ቢያሳውቁም ይኅን ያኅል አላሉም፡፡