ሙሽሪት ከ25 ዓመት በታች ከሆነች 1 ሺህ ዩዋን የሚለግሰው የቻይና ግዛት – ቻንግሻን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና ዜጂያንግ ክልል ቻንግሻ ግዛት ሙሽሪት ከ25 ዓመት በታች ከሆነች ለጥንዶቹ 1 ሺህ ዩዋን የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጣቸው አስታወቀ፡፡
በምስራቅ ቻይና የሚገኘው ቻንግሻ ግዛት “ዊ ቻት” በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ÷ ማበረታቻው ከዕድሜ ጋር የሚስማማ ጋብቻ እና ልጅ መውለድን ለማበረታታት ያለመ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በግዛቱ ዝቅተኛው የሕጋዊ ጋብቻ ዕድሜ ለወንዶች 22 ሲሆን÷ ለሴቶች ደግሞ 20 መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ለሽልማቱ ብቁ ለመሆንም ከጥንዶቹ አንዱ በቻንግሻን ግዛት ውስጥ የቤተሰብ ምዝገባ ወይም በሀገሬው አገላለፅ “ሁኩዎ” ሊኖረው እንደሚገባ ነው የተመለከተው፡፡
ግዛቱ ልጆች ላሏቸው ጥንዶች የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን እንደሚሰጥም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም በግዛቱ ውስጥ ለተወለዱ 2ኛ እና 3ኛ ልጆች በየዓመቱ የ5 ሺህ እና 10 ሺህ ዩዋን ድጎማ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም 3 ልጆች ላሏቸው ሴቶች ነፃ ዓመታዊ የማህፀን ምርመራን እንደሚጨምር ተብራርቷል፡፡
ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ 2 ወይም ከዚያ በላይ ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦችም ነፃ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ነው ግዛቱ ያስታወቀው፡፡
በቻይና ዜጎች በወቅቱ እንዲያገቡና ልጅ እንዲወልዱ ግፊት ማድረግ የተጀመረው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በስድስት አስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ መሆኑን ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Like
Comment
Share