Fana: At a Speed of Life!

በአንድነት ስንሰራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የአትሌቶቻችን ድል አድራጊነት ማሳያ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድነትና በመተባበር ስንሰራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የአትሌቶቻችን ድል አድራጊነት ማሳያ ነው ሲል የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኢትዮጵያ በሀንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበችውን ድል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫው እንደተጠቀሰው ÷የቡድፔስቱ መድረክ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ እንደወትሮው ሁሉ ከፍ ብሎ የተውለበለበበት መድረክ ነበር፡፡

ከድሉ ባሻገር የነበረው የቡድን ሥራ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ያኮራና አንጸባራቂ ድል እንደነበርም በመግለጫው ተነስቷል፡፡

“አረንጓዴው ጎርፍ” እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፤ ዘንድሮም ስያሜውን በሚመጥን መልኩ አትሌቶቻችን ተከታትለው በመግባት የሀገራችንን የድል ታሪክ ደግሟል ሲልም ያትታል መግለጫው፡፡

በተለይ በሴቶች 10 ሺህ ሜትርና በማራቶን ሩጫ የታየው የቡደን ሥራ፣ እርስ በእርስ መናበብ እና መረዳዳት ከድል ምክንያትነቱ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ተዓምር መሥራት እንደምንችል ያሳየ ነው ብሏል፡፡

አትሌቶቻችን በሩጫ ወቅት መረጃ በመለዋወጥ፣ በመተጋገዝ እና አንዳቸው ሌላውን በመጠበቅ እስከመጨረሻው ድረስ በቡድን መጓዛቸው የሚደነቅ እንደሆነም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ሀገራችን ውድድሩ 2 የወርቅ፣ 4 የብር እና 3 የነሀስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ሆና ውድድሩን በማጠናቀቅ በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ስንቅ የሚሆኑ ተሞክሮዎች ማግኘቷም ተመላክቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአትሌቲክስ ውድድሮች ጠፍቶ የነበረው የኢትዮጵያውያን የቡድን ሥራ በዘንድሮው ውድድር በጉልህ መታየቱ በዘርፉ ያለንን ስኬት በቀጣይ ጊዜያት ለማሻሻል የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ከምንም በላይ ከውጤቱ ባሻገር ውጤቱ የተገኘበት መንገድ ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያስደሰተ፤ የሀገራዊ አንድነታችን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ አኩሪ ድል መሆኑ በመግለጫው ተነስቷል፡፡

ሀገርን በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች በመወከል ድል ማስመዝገብ የሚወደስ ተግባር ነውያለው አገልግሎቱ ሀገራችን ከጊዜያዊ አሉታዊ ፈተናዎች ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች ድል የሚያደርጉ የትጉሃን ሀገር መሆኗን ለዓለም ማሳየት በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በጥረታቸው ድል የሚያደርጉ፣ የሀገራቸውን መልካም ገፅታ አጉልተው የሚሳዩ የብርቅዬ ልጆች ቤት መሆኗ ዛሬም በዓለም አደባባይ ታይቷል ሲልም ያትታል መግለጫው፡፡

ኢትዮጵያ ከፈተናዋ በላይ ተስፋዋ የለመለመ፣ አዎንታዊ ስኬቷም በእጅጉ እንደሚልቅ በተለያዩ ዘርፎች እየታየ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በስፖርት ዘርፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የቀጠለው የአሸናፊነት ገድል በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ በመግለጫው መልዕክት መተላለፉን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.