የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ላበረከተው አስተዋፅዖ ዕውቅና ተሠጠው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሶማሊያ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ተልዕኮ ተቀብሎ ላበረከተው አስተዋፅዖ ዕውቅና ተሠጥቶታል፡፡
ሠራዊቱ በተለይም በአል-ሸባብ የሽብር ቡድን ሠላም ርቆት የቆየውን የሶማሊያ ሂራን ክልል ሂርሻቤሌ አካባቢን ከሽብር ቡድኑ ጥቃት ነፃ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በሶማሊያ የአንድ ዓመት የተልዕኮ ቆይታቸውን ላጠናቀቁ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትም የሜዳሊያ ሽልማት እና ዕውቅና መሠጠቱን በሶማሊያ የአፍሪካ ጊዜያዊ ተልዕኮ ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ጊዜያዊ ተልዕኮ የሎጂስቲክስና ድጋፍ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ፒተር ኪማኒ ሙቴቲ በእውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ማሃስ ወረዳ የኅብረቱን ተልዕኮ ተቀብሎ በአንድ ጀምበር የፈጸመው ጀብዱ እጅግ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከጂቡቲ እና ሶማሊያ መከላከያ ሠራዊቶች ጋር በመቀናጀት በቤሌቴዌይን፣ ሃልጋን ፣ ማሃስ ሂራን እና ጋልጋዱድ አካባቢዎች እና ክልሎች አኩሪ ገድል መፈጸማቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሐመድ፣ የሂራን ክልል ገዢ አብዱላሂ መአሊን፣ የኅብረቱ ጊዜያዊ ወታደራዊ ተልኮ ዋና አዛዥ ብሪጋዲየር ጀኔራል ተገኝ ክንዱ ገዙ፣ የሴክተር አራት አዛዥ ኮሎኔል ሐሰን ጃማ ፣ የቤሌቴዌይን ከተማ ከንቲባ ናዳር ታባህ እንዲሁም የተለያዩ የተመድ እና በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ባለሥልጣናት በእውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ተገኝተዋል፡፡