Fana: At a Speed of Life!

ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፍ ትብብር መጠናከር እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ የሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ “የአፍሪካን የአካባቢ ችግሮች ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም፣ ትብብርን ማጎልበት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአካባቢ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአካባቢ ጥበቃ ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በጉባኤው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደገለጹት÷ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ የመሬት መራቆት፣ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋና በረሃማነት አስከትሏል።

የአየር ንብረት ለውጥ የአህጉሪቱን ዜጎች ለተለያዩ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች መዳረጉን ገልጸው÷ በተለይም የምግብ ዋስትን ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጓል ብለዋል፡፡

ይህም አህጉሪቱ የ2033 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ለመከላከል በትብብር መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በዜጎቿ ተሳትፎ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርኃ-ግብር በመቅረጽ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታዋን እያጠናከረች እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.